Tuesday, March 26, 2013



                           ዐቢይ ጾም፤ ወደ ትንሣኤ የሚደረግ ጉዞ
አንድ ሰው ለጉዞ ሲነሣ ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ አለበት፡፡ በዐቢይ ጾምም እንዲሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ዐቢይ Jesus.JPGጾም መንፈሳዊ ጉዞ ነው፤ መድረሻውም ትንሣኤ ነው፡፡ ለእውነተኛው መገለጥ ለፋሲካ መሟላት የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነና ስለ ክርስትና እምነታችንና ሕይወታችን በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ስለሚገልጥልን ይህን በዐቢይ ጾም እና በትንሣኤ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት በመሞከር መጀመር አለብን፡፡

የትንሣኤ በዓል ከበዓላት አንዱ ከመሆን እና የአንድ ያለፈ ክስተት መታሰቢያ ከመሆን በላይ ሊታሰብ ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ጊዜም ብቻ እንኳን ቢሆን የትንሣኤን በዓል በሚገባው መልኩ አክብሮ በዚያም ከቀን ይልቅ በሚያበራው ሌሊት የተሳተፈና ያንን ልዩ ደስታ የቀመሰ ማንም ሰው ያውቀዋል፡፡ ያ ደስታ ግን ስለ ምንድን ነው? በትንሣኤ በዓል ዕለት እንደምናደርገው «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሀጺባ በደመ ክርስቶስ»፤ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ»፣ «ዛሬ ሁሉም ነገር፣ ሰማይም፣ ምድርም፣ ከምድር በታች ያሉ ነገሮችም በብርሃን ተሞሉ» እያልን መዘመር የምንችለው ለምንድነው? «የሞት መሞት፤ የሲኦል መበዝበዝ፣ የአዲስና የዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ...» እያልን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ይህ ነው፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ከመቃብር ወጥቶ ያበራው አዲስ ሕይወት በክርስቶስ ለምናምን ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ «በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ.6:4/ እንዳለው ይህ አዲስ ሕይወት እና ብርሃን ለእኛ የተሰጠን በጥምቀታችን ዕለት ነው፡፡

ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር፣ የክርስቶስን ትንሣኤ በእኛ ላይ እንደ ተደረገ እና አሁንም እንደሚደረግ አድርገን እናከብራለን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳችን የዚያን የአዲስ ሕይወት ስጦታ እና ያንን የምንቀበልበት እና በእርሱም የምንኖርበትን ኃይል ተቀብለናል፡፡ ይህ ስጦታ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር ሁሉ ስለ ሞትም ጭምር ያለንን አመለካከት የሚቀይር ነው፡፡ በደስታ «ሞት የለም» ብለን በእርግጠኝነትም መናገር እንድንችል የሚያደርገን ነው፡፡

ኦ! ሞት ግን አሁንም አለ፤ በእርግጠኝነት እንጋፈጠዋለን፤ አንድ ቀንም መጥቶ ይወስደናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በራሱ ሞት፣ የሞትን ባሕርይ /ምንነት/ እንደቀየረው ይህ ሙሉ እምነታችን ነው፤ ሞትን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ፣ ማለፊያ፣ ፋሲካ አድርጎታል፤ ከአሳዛኝ ነገሮች ሁሉ የበለጠ አሳዛኝ የነበ ረውን ሞት ወደ ፍጹም ድልነት ቀይሮታል፡፡ «ሞትን በሞቱ ደምስሶ» የትንሣኤው ተካፋዮች አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው «ክርስቶስ ተነሥቷል፣ ሕይወትም ሆኗል፤ ማንም በመቃብር አይቀርም» የምንለው፡፡

ቁጥር በሌላቸው በቅዱሳኖቿ የተረጋገጠውና ግልጽ የተደረገው የቤተክርስቲያን እምነት ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እምነት በእኛ ውስጥ ሁልጊዜ አለመኖሩ [ይህንን ሁል ጊዜ አለማሰባችን]፤ እንዲሁም እንደ ስጦታ የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት ሁልጊዜ መጣላችንና መካዳችን እንዲሁም ክርስቶስ ከሞት እንዳልተነሣ ሆነን የመኖራችን ነገር እና ያ ልዩ ክስተት ለእኛ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው መሆኑ የዕለት ተዕለት ተሞክሮአችን አይደለምን?
ይህ ሁሉ የሆነው በድካማችን ምክንያት ነው፡፡ ማለትም ጌታ «አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ» ባለን ጊዜ በወሰነልን ደረጃ «በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር» መኖር ለእኛ የማይቻለን በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ በቀላሉ እንረሳዋለን፤ ምክንያቱም ሁልጊዜም በተለያዩ ሥራዎች የተጠመድን እና በዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን የተዋጥን ነን፤ ስለ ምንረሳም እንወድቃለን፤ በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት እና ብርሃንም እንጠራለን፡፡

በዚህ በመርሳት፣ በመውደቅ እና ኃጢአት በመሥራት በኩልም ሕይወታችን በድጋሜ «አሮጌ» ይሆናል፤ ጥቅም /ረብ/ የሌለው፤ ጨለማ እና ትርጉም አልባ፤ ትርጉም የሌለው ጉዞ፤ ትርጉም ወደሌለው ፍጻሜ ይሆናል፡፡
ሞትን እንኳን ሳይቀር ረስተነው ከቆየን በኋላ በድንገት «ደስታ በሞላበት ሕይወታችን» መሐል አስፈሪ፣ ሊያመልጡት የማይችሉት እና አስጨናቂ ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል፡፡
በየጊዜው ኃጢአታችንን ልንናዘዝ እንችላለን፤ ነገር ግን ሕይወታችንን ከዚያ ክርስቶስ ለእኛ ከገለጠውና ከሰጠው ከአዲሱ ሕይወት ጋር ማዛመድና ሕይወታችንን በዚያ ላይ መመሥረት እናቆማለን፡፡ ትልቁና እውነተኛው ኃጢአት፣ የኃጢአቶች ሁሉ ኃጢአት፣ የስም ብቻ የሆነው ክርስትናችን በጣም አሳዛኝ ገጽታ ይህ ነው፡፡ የሕይወታችንን ትርጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ አለመመሥረት፡፡

ይህንን ልብ ካልን፣ የትንሣኤ በዓል ምን እንደሆነና ዐቢይ ጾም ለምን ከእርሱ በፊት እንዲኖር እንዳስፈለገ እንረዳለን፡፡
በዐቢይ ጾም በቤተክርስቲያን የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ዓላማም በቀላሉ የምንጥለውንና የምንወስደውን የዚያን የአዲስ ሕይወት ርእይ እና ጣዕም በውስጣችን እንድናድሰው ለመርዳት እና ተጸጽተን ወደ እርሱ እንድንመለስ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የማናውቀውን ነገር እንዴት ልንወድና ልንፈልግ እንችላለን? አይተነው እና አጣጥመነው የማናውቀውን ነገር እንዴት በሕይወታችን ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ ልናደርገው እንችላለን? በአጭሩ ስለ እርሱ ምንም አሳብ የሌለንን መንግሥት እንዴት ልንፈልግ እንችላለን? አንችልም፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሥርዓተ አምልኮዎች ይህን እንድናደርግ ትረዳናለች፡፡

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወዳለው ሕይወት መግቢያችን፤ ከዚያም ጋር ያለን ኅብረት መሠረት በቤተክርስቲያን ያለው አምልኮ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን «ጆሮ ያልሰማውን፣ ዓይንም ያላየውን በሰው ልብም ያልታሰበውን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት ያዘጋጀውን» ከዚያ ነገር ጥቂቱን ለእኛ የም ትገልጥልን በአምልኮ ሕይወቷ አማካኝነት /through her liturgical life/ ነው፡፡ በዚያ በአምልኮ ሕይወት መሐል ላይ ደግሞ፣ እንደ  ጠቅላላው የአምልኮ ሥርዓት ልብ እና ከፍታ፣ እንዲሁም ጨረሮቿ ሁሉም ቦታ እንደሚደርሰው ፀሐይ ሆኖ የትንሣኤ በዓል ይቆማል፡፡
የትንሣኤ በዓል በየዓመቱ ወደ ክርስቶስ መንግሥት ግርማ እና ውበት ለማሳየት የሚከፈት በር ነው፡፡ የሚጠብቀን ዘለዓለማዊ ደስታ ቅምሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በስውር ቢሆንም ፍጥረትን ሁሉ የሞላው፣ «ሞት የለም!» የሚለው የዚያ ድል ክብር መገለጫ ነው፡፡

አጠቃላይ የቤተክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ዓመታዊው የአምልኮ መርኀ ግብር /liturgical year/ የተደራጀው በትንሣኤ ዙሪያ ነው፤ ማለትም በዓመቱ በተከታታይ የሚመጡት ወቅቶች እና በዓላት ወደ ፋሲካ፣ ወደ ፍጻሜው የሚደረጉ ጉዞዎች ይሆናሉ፡፡ ፋሲካ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ጅማሬም ነው፤ «አሮጌ» የሆነው ነገር ሁሉ ፍጻሜ እና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፤ ከዚህ ዓለም በክርስቶስ ወደ ተገለጠው መንግሥት መሸጋገሪያ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኃጢአት እና የማይረቡ ነገሮች መንገድ የሆነው «አሮጌው» ሕይወት ግን በቀላሉ የሚሸነፍ እና የሚቀየር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊፈጽመው የማይችለውን ነገር የወንጌል ሕግ ትጠብቅበታለች፡፡ ከአቅማችን እና ከምንችለው እጅግ በጣም በሚበልጥ ርእይ፣ ግብ እና የሕይወት መንገድ እንፈተናለን ምክንያቱም ሐዋርያት እንኳን ሳይቀሩ የጌታን ትምህርት ሲሰሙ ተስፋ በመቁረጥ «ይህ እንዴት ይቻላል?» ብለው ጠይቀውታል፡፡ በእርግጥም በየዕለቱ በሚያስፈልጉን ነገሮች በመጨነቅ፣ ቀላል ነገሮችን፣ ዋስትናን እና ደስታን በመፈለግ የተሞላን የማይረባ የሕይወት እሳቤ ትቶ «ሰማያዊ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ» የተባለለትንና ከፍጽምና በቀር ሌላ ምንም ግቡ ያልሆነውን የሕይወት እሳቤ መያዝ ቀላል አይደለም፡፡

ዓለም በመገናኛ ብዙኃኖቿ በሙሉ «ተደሰቱ፣ ቀለል አድርጋችሁ እዩት /take it easy/፣ ሰፊውን መንገድ ተከተሉ» ትለናለች፡፡ ክርስቶስ ደግሞ በወንጌል «ጠባቡን መንገድ ምረጡ፣ ተዋጉና መከራን ተቀበሉ፤ ይህ ወደ እውነተኛው ደስታ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ነውና» ይለናል፡፡ ቤተክርስቲያን ካልረዳችን ካልደገፈችን እንዴት ያንን አስጨናቂ ምርጫ መምረጥ እንችላልን? እንዴትስ መጸጸት /ንስሐ መግባት/ እና በየዓመቱ በትንሣኤ በዓል ዕለት ወደሚሰጠው የከበረ ቃል ኪዳን መመለስ እንችላለን? የዐቢይ ጾም አስፈላጊነቱ እዚህ ላይ ነው ይህ በቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀልን ዕርዳታ፣ የትንሣኤ በዓልን የመብላት የመጠጣት እና የመዝናናት ፈቃድ የሚገኝበት ዕለት ነው ብለን ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለው የአሮጌው መጨረሻ እና የእኛ ወደ አዲሱ መግቢያ አድርገን እንድንቀበለው የሚያስችለን የንስሐ ትምህርት ቤት ነው፡፡

በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም ዋና ዓላማ ንኡሰ ክርስቲያንን ማለትም አዳዲስ አማንያንን በዚያን ጊዜ በትንሣኤ ዕለት ለሚፈጸመው ጥምቀት ማዘጋጀት ነበር፡፡ ነገር ግን /ክርስትና ከተስፋፋና/ የሚጠመቁ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰ በኋላም ግን ቢሆን የዐቢይ ጾም መሠረታዊ ትርጉም በዚያው ጸንቷል፡፡ ስለዚህም ትንሣኤ በየዓመቱ ወደ ጥምቀታችን መመለሻ ሲሆን ዐቢይ ጾም ደግሞ ለመመለስ መዘጋጃችን ነው፤ በክርስቶስ ወደሆነው አዲስ ሕይወት ለመተላለፍ የምናደርገው ትጋትና ጥረታችን ነው፡፡

ዐቢይ ጾም ጉዞ ነው፤ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ስንጀምረው፣ በዐቢይ ጾም ብሩህ ሐዘን /bright sadness/ ውስጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ስንራመድ ከር. . . ቀት ፍጻሜውን /መጨረሻውን/ እናያለን፡፡ ይህም የትንሣኤ በዓል ደስታ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ክብር መግባት ነው፡፡ የዐቢይ ጾምን ሐዘን ብሩህ የሚያደርገውና በወቅቱ የምናደርገውን ጥረት «መንፈሳዊ ምንጭ» የሚያደርገውም ይህ የትንሣኤ በዓል ቅምሻ የሆነው ብሩህ ርእይ ነው፡፡
ሌሊቱ ጨለማ እና ረጅም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመንገዱ ሁሉ ምስጢራዊ የሆነ ብሩህ ወገግታ በአድማሱ ላይ ያንፀባርቃል፡፡«ሰውን ወዳጅ /መፍቀሬ ሰብእ/ ሆይ! አቤቱ ተስፋ ያደረግነውን ነገር አታስቀርብን» አሜን፡፡

Monday, March 11, 2013


 ቶም እና ጄሪ


«ቶም እና ጄሪ» ፊልም ዊልያም ሐና እና ዮሴፍ ባርባራ በተባሉ ባለሞያዎች ለሜትሮ ጎልድዊን ካምፓኒ የተሠራ ተከታታይ የካርቱን ፊልም ነው፡፡ የቤት ውስጥ ድመት በሆነው በቶም እና በተንኮለኛዋ አይጥ በጄሪ መካከል በማያቋርጥ ቅንቃኔ እና ጠላትነት እየተቀጣጠለ የሚሄደው ይሄ ፊልም፣ አስገራሚም አስቂኝም ነው፡፡ በ1940 እኤአ የተጀመረው ቶም እና ጄሪ፣የአኒሜሽኑ ኩባንያ እስከ ተዘጋበት እስከ 1957 እኤአ ብቻ 114 ያህል ተከታታይ ፊልሞችን በሐና እና በባርባራ ደራሲነት እና አዘጋጅነት አቅርቧል፡፡

በ1960 እኤአ በአዲስ መልክ ፊልሙ እንደ ገና መዘጋጀት እና መታየት ጀመረ፡፡ ዛሬ በታይም ዋርነር ካምፓኒ ባለቤትነት እና በዋርነር ብሮስ አከፋፋይነት የተያዘው የቶም እና ጄሪ የካርቱን ፊልም 162 ተከታታይ ፊልሞችን ያጠቃልላል፡፡

ቶም እና ጄሪ አብረው በአንድ ሰው ቤት ውስጥ የሚኖሩ ነገር ግን መቼም ቢሆን ተስማምተው የማያውቁ ፍጡራን ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ በጥቅም ምክንያት ሲስማሙ እንኳን በአከፋፈሉ ምክንያት ለመጣላት ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡ ሁለቱንም የሚቃረን ነገር ከመጣ ግንባር የሚፈጥሩት ቶም እና ጄሪ፣ የጋራ ጠላታቸውን ለየራሳቸው ምክንያት ሲሉ ካጠቁ በኋላ እንደገና እርስ በርሳቸው መጣላት ይቀጥላሉ፡፡

ይህ፣ መቼም የማያባራ የቶም እና የጄሪ የቅንቃኔ እና የጠላትነት ፊልም፣ በባለቤቶቹ ዘንድ የታወቁ 162 ተከታታይ ፊልሞች አሉት ቢባልም ጠቅላላ የፊልሞቹ ብዛት ግን ከዚህ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ 163ኛው ፊልም የሚዘጋጀውም፣ የሚሠራውም፣ የሚቀርበውም እኛው ሀገር ነው፡፡ ፊልሙን የደረሱትም፣ የሚያዘጋጁትም፣ የሚተውኑትም የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ናቸው፡፡

ቶም እና ጄሪ በአንድ ሰው ቤት የሚኖሩ ባላንጣዎች ናቸው፡፡ የ1960ዎቹ የሀገራችን ትውልዶችም በአንድ ወቅት የተነሡ የአንዲት ሀገር ልጆች ናቸው፡፡ የተነሡበት ዓላማም ተመሳሳይ ነው፡፡ እነርሱ በሚያስቡት መንገድ ብቻ ሀገሪቱን ማሳደግ፡፡ የርእዮተ ዓላማቸውም ቤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ያም የብዕር ስሙ ይለያይ እንጂ ከኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ አይዘልም፡፡ ፀር፣ትግል እና ግንባር ይወዳሉ፡፡

ዛሬ በሀገሪቱ የወዲህም ሆነ የወዲያ ጎራ፣በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስጶራ የሚገኙ፤ የፖለቲካው እና የቤተ እምነቱን መዘውር የሚዘውሩ አካላት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከ1960 እስከ 1970 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ የተነሡ፤ በዚያ ዘመን በነበሩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተማረኩ፣ የዚያን ዘመን የፖለቲካ አመለካከቶችን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ናቸው፡፡

ወይ ኢሕአፓ፣ወይ ኢዲዩ፣ወይ መኢሶን፣ወይ ኢሠፓ፣ወይ ኢጭአት፣ወይ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ ወይ የሠራተኞች ንቅናቄ፣የላብ አደር ፓርቲ፣ኢማሌድኅ፣ሰደድ ወዘተ ውስጥ ገብተው ሲቆራቆሱ እና ሲተረማመሱ፤ አንዱ ሌላኛውን ለማጥቃት ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ሲያካሂዱ፣ አብዮታዊ ርምጃ ሲወስዱ እና ተቀናቃኞቻቸውን አብዮታዊ ምት ሲመቱ የነበሩ ናቸው፡፡

በውይይት ክበብ፣ በማሌ ጥናት፣በስብሰባ አካሄድ፣በፓርቲ አመሠራረት፣ጭቁኑን ሕዝብ በማታገል መርሕ አልስማማ ብለው ወይ ተጣልተዋል፣ ወይ ተኳርፈዋል፣ ወይ ተለያይ ተዋል፣ወይ ተፈላልገዋል፣ወይ ቂም ተያይዘዋል፣ ወይ ጥርስ ተነካክሰዋል፡፡ ስለዚህም እንደ ቶም እና ጄሪ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እያየ ከመቀናቀን የተሻለ ሌላ ፊልም ለመሥራት ያዳግታቸዋል፡፡

«የምጠላው ወይም የምቃወመው አታሳጣኝ» ብለው የተሳሉ ይመስል ያለ ጠላት መኖር አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቶም፣ ድሮ ጄሪ ያደረገችበትን ተንኮል ፊልሙን መልሶ እያየ ይበሳጫል፡፡ ከመበሳጨትም አልፎ ለመበቀል እርሷን ፍለጋ ይሄዳል፡፡ እነዚህም ከስድሳ ስድስት እስከ ሰባ ዓም የተቀረጸውን የደም መፋሰስ ፊልም ደጋግመው እያዩ አንዱ ሌላውን በኋላ ታሪኩ ምክንያት ለማጥቃት ይፈላለጋሉ፡፡

162 ፊልሞች ሲሠሩ ቶምም ሆነ ጄሪ አሁንም የፊልሙ ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው፡፡ አልተ ቀየሩም፡፡ ከ1940 እስከ 2009 ፊልሙን የሚሠሩት ቶም እና ጄሪ ናቸው፡፡ አልተለወጡም፡፡ በ1960ዎቹ የነበሩት ልጆች ያዩት የቶም እና ጄሪ ፊልም ዛሬም በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያሉ ልጆችም ያዩታል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክም ፊልሙ እንደ ቶም እና ጄሪ አልተቀየረም፡፡ ያው ነው፡፡ በ1960ዎቹ የነበሩት የሀገራችን የፖለቲካ ቶም እና ጄሪዎች ዛሬም አሉ፡፡ የፖለቲካው ፊልም ዋነኛ ተዋናዮች እነርሱው ናቸው፡፡ አሁንም ሀገሪቱ ከ1960ው ትውልድ ተጽዕኖ መላቀቅ አልቻለችም፡፡ መቼ ይሆን ከስድሳዎቹ ወጥተን ወደ ሰባዎቹ፣ ወደ ሰማንያዎቹ፣ ወደ ዘጠናዎቹ እና ወደ ሁለተኛው ሺ የምንገባው? አሁንምኮ በየፖለቲካው መድረክ የምናያቸው ትክለ ሰብእናዎች የዛሬ ሠላሳ ዓመት የነበሩትን ነው፡፡

አዲሱ ትውልድም የቶም እና ጄሪ ፊልምን ስለለመደ በተመሠረቱት ነገሮች ሁሉ እነዚህን አካላት ካላካተተ፤ ወይንም እነዚህ አካላት ቡራኬ ካልሰጡት በቀር ይሳካል ብሎ ማመን ያቆመ ይመስለኛል፡፡

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ

ተብሎ በተዘፈነባት ሀገር፣ዛሬ ዛሬ ገበየሁም አይሞት ባልቻም አይተካ፡፡

ቶም እና ጄሪ ቦታ ይቀያየራሉ እንጂ ስልትም መንገድም አይቀይሩም፡፡ ውጭ የነበረው ቶም ቤት ሲገባ ጄሪ ከቤት ትባረራለች፣ያለበለዚያም ጄሪ ቤት ገብታ ቶም ይባረራል፡፡ ዛሬ የአንድ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበረው ነገ የሌላ ይሆናል፤ የአንድ ፓርቲ ልሳን ሲያዘጋጅ የነበረው ምንም ዓይነት የአመለካከት ለውጥ ሳያደርግ ሌላው ጋር ይቀላቀላል፡፡ ደንበኛ ጥናት አድርገን ብንፈትሽ ዛሬ የቆሙለትን ዓላማ ደግመው ደጋግመው ሲቃወሙት የነበሩ አስገራሚ ቶም እና ጄሪዎችን በሀገራችን ታሪክ እናገኝ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ አመለካከታቸው የሚወሰነው እንደሚያምኑበት ነገር ሳይሆን እንደ ሚገቡበት ድርጅት እና እንደሚሠጣቸው ሥልጣን ነው፡፡

ቶም እና ጄሪን የሚያስማሟቸው ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ጥቅም ሲሆን ሁለተኛው የጠላት መኖር ነው፡፡ በኛም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ይሄው ፊልም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ቶሞች እና ጄሪዎች አንድ የሚሆኑት ጥቅም እስከተገኘ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ጥቅም ከተገኘ በርእዮተ ዓለሞቻቸው ላይ እንኳን የረባ ውይይት ሳያደርጉ፤ የቱጋ የአቋም ለውጥ እንዳደረጉ በሚገባ ሳይረዱም ሳያስረዱም በቅጽበት ይቀናጃሉ፣ ይተባበራሉ፤ ይዋሐዳሉ፣ግንባር ይመሠርታሉ፡፡ አከፋፈል ላይ ሲለያዩ ደግሞ የተባበሩ ቀርቶ የተጎራበቱ መሆናቸውን እስክንጠራጠር ድረስ ይናከሳሉ፡፡

ቶም እና ጄሪ ጠላት መጣብን ብለው ሲያስቡ አንድ ሆነው ያባርሩትና ከጠላታቸው በባሰ መልኩ እርስ በርሳቸው ይባላሉ፡፡ የሀገራችን ቶሞች እና ጄሪዎችም ሊያጠፋን ነው ብለው የሚያስቡት ጠላት ሲያጋጥማቸው አብረው ይሰበሰባሉ፣ይወስናሉ፣መግለጫ ያወጣሉ፣ ይሰለፋሉ፡፡ በኋላ ግን ጠላት ነው ብለው ከሚያስቡት አካል በባሰ ሁኔታ እርስ በርሳቸው መበላላት ይቀጥላሉ፡፡

ለቶም እንደ ጄሪ፣ለጄሪም እንደ ቶም የሚቀርባቸው የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለቶም እንደ ጄሪ፣ ለጄሪም እንደ ቶም የሚጎዳቸው የለም፡፡ የኛም ፖለቲከኞች ይህንኑ ፊልም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ 163ኛውን ክፍል፡፡

ባለፈው ጊዜ የዘመን አቆጣጠራችንን ብቻ ተመልክተን ሁለተኛውን ሺ አከበርነው እንጂ የፖለቲካ አቆጣጠራችን ብናየው ኖሮ ወደ ሁለተኛው ሺ ለመግባት ቢያንስ ገና ሠላሳ ያህል ዓመታት በቀሩን ነበር፡፡ አሁንም ተቃውሞ እና ጠላትነትን አልለየንም፣ አሁንም ገና ደጋፊነትን እና ምእመንነትን አልለየንም፡፡ ተቃዋሚያችን ምንም ዓይነት በጎ ነገር ቢያስብ ከመቃወም አንመለስም፤ ጠላትነት እንጂ ተቃውሞ አናውቅማ፡፡ የምንደግፈው አካልም ምንም ዓይነት ጥፋት ቢያጠፋ ከማመስገን ወደ ኋላ አንልም፤ ምእመንነት እንጂ ድጋፍ አናውቅማ፡፡ አይቶም እና ጄሪ፡፡

ሰሞኑን እዚህ ኔዘርላንድ በአንዳች ምክንያት የተጣሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጎራዎችን ለማስታረቅ የተሰየሙ የሀገሬ ሽማግሌ ያሉኝን እዚህ ላይ ብጠቅሰው እንዴት ጥሩ ነው፡፡ አንደኛው ወገን ከሌላው ወገን ጋር ለመታረቅ በቅድመ ሁኔታነት አሥራ አምስት ነጥቦችን ያስቀምጣል፡፡ ሽማግሌዎቹም ይህንኑ ይዘው ወደዚያኛው ጎራ ይሄዱና ጉዳዩን ያቀርባሉ፡፡ እነዚህኞቹም ቡድኖች ከተወያዩ በኋላ አሥራ አምሱንም ነጥቦች በሙሉ እንቀ በላለን ብለው መልስ ይሰጣሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም ድካማቸው ፍሬ በማፍራቱ ተደስተው ወደነዚያኞቹ ይሄዱና «እነዚያኞቹ በሃሳባችሁ ሙሉ በሙሉ ተስማምተዋል» ይሏቸዋል፡፡ ሰዎቹ አላመኑም «አሥራ አምስቱንም ነገር ተቀበሉት?» ይላሉ፡፡ «አዎ ሁሉንም ተቀብለዋል»፡፡ «እንዴት አንድ ሁለቱን እንኳን አልተቃወሙም፤ አንዳች ነገር ቢያስቡ ነውና እንዲያውም አንታረቅም» ብለው መልሱን አሉኝ፡፡

እውነታቸውን ነው፡፡ ቶም እና ጄሪአይደሉ፤ አንዳች የሚያጣላ፣ የሚያቆራቁስ፣ ለፓል ቶክ፣ ለዌብ ሳይት እና ለወሬ የሚሆን የጠብ መነሻማ ያስፈልጋቸዋልኮ፡፡ ተስማምተው ከሠሩ ምን ሊውጣቸው ነው? በኋላ በምን ተለያየን ሊሉ ነው፡፡ አይ ቶም እና ጄሪ፡፡

ኢትዮጵያዊውን የቶም እና ጄሪ ፊልም ከቁጥር አንድ ጀምራችሁ የምትተውኑ የፖለቲካ ቶም እና ጄሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት በቃን ብትሉ ምናለ? ቢያንስ ለአፋችሁ ያህል፡፡ ሀገሪቱ 1960ዎቹን ለቅቃ ወደ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ትገባ ዘንድ ብትረዷት ምናለ፤ በአንድ ወቅት በአንድም በሌላም መልኩ የቶም እና ጄሪን ፊልም የጀመራችሁ ተዋንያን፣ እባካችሁ ሌላ ፊልም እንይበት፡፡ የመነካከስ እና የመበላላት፣ የማያቋርጥ ቅንቃኔ እና ጠላትነት ተከታታይ ፊልም ሰልችቶናል፡፡

ሮተርዳም፣ኔዘር ላንድ

 ይቅርታና ይቅር ባይነት




ወንድም ዲ/ን ዳንኤል እንደወትሮው ሁሉ እጅግ ጠቃሚ ጉዳይ ነው ያነሳኸው። ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችን ይህንን ፀጋህን ይበልጥ ያብዛልህ፤ አሜን።

ይቅርታ ወይም ይቅር ባይነት የሰው ልጅ በዚህ ዓለም በሚኖርበት ወቅት በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስሮች ወይም ግንኙነቶች አማካኝነት ከሌሎች የማኅበረሰቡ  ክፍሎች ጋር ለሚኖረው ጤናማ የኑሮ ጥምረት ትልቅ ድርሻ አለው ብዬ አምናለሁ። ይቅር መባባል ያለፈ በደልን አጥቦና አስወግዶ ለቀሪው ህይወት አዲስ ልቡናን በመፍጠር ግንኙነታችንን ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል። በአንድ ወቅት በታሪክ አጋጣሚ ተበዳድለው፣ ተቀያይመው፣ ተኮራርፈው ከዚያም ባለፈ ደም ተቃብተው እና ለቂም በቀል ሌት ተቀን በሃሳብም በግብርም ይሯሯጡ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በልቡናቸው የተቋጠረውን የመጠፋፋት ሕልምና ዕቅድ ወደ ጎን ትተው  አንዱ ካንዱ በጋብቻ እስከመጣመርና አንዱ ላንዱ ዋስ ጠበቃ እስከመሆን ያደርሳቸዋል። በዚሁ መልካም አጋጣሚ ምክንያትም ሊጠፋ የነበረው ሕይወት፣ ሊፈስ የነበረው ደም እና ሊጎድል የነበረው አካል ከጥፋት፣ ከመፍሰስና ከመጉደል ይድናል።


ከዚህም ባለፈ ቂም በቀል በይቅርታ እስካልተደመደመ ድረስ ጥፋቱ መቋጫ የለውም። አንዱ ላለፈ በደሉ አዲስ በደል ሲፈፅም ሌላኛውም አፀፋውን ሲመልስ የሁለቱም ወገኖች በምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ መጠፋፋቱ ይቀጥላል። እንዲህ ዓይነቱ ለይቅርታ ቦታ አለመስጠት በተለይ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ በእኛ በኢትዮጵያውያን ይብሳል። ምክንያቱ ምን ይሆን? በምጣኔ ሃብት አለማደጋችን፣ በቴክኖሎጂ አለመበልፀጋችን ወይም ገና ያልደረስንበትና ያልተማርነው ዘመናዊ ትምህርት ይኖር ይሆን? ትልቁ መንስዔ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል እንዳልሆነ የምንገነዘበው እነዚህ ምክንያትች ሞልተው የተትረፈረፉላቸው ወገኖቻችን ይባስ ብለው የችግሩ ሰለባ እነሱ መሆናቸው ነው።

ያደግንበት ማኅበረሰብም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በእትንኩኝ ባይነትና ክንዴን ሳልንተራስ እንዴት እደፈራለሁ? አስተሳሰቡ በደንብ አድርጎ አጥምቆናል። ገና ከእናታችን ማኅፀን ከመውጣታችንም ደም መላሽ ብሎ ስም ያወጣልናል። አንደበታችን እማማ አባባ ማለት ሳይጀምር በቂም በቀል ዲፕሎማ ከቤተሰባችን እና ከአካባቢያችን በከፍተኛ ማዕረግ እንመረቃለን። ከዚያ በኋላ ልክ ግብፃውያን እናቶች ልጆቻቸውን አባይ ሕይወትህ ነው እያሉ እንደሚያሳድጉት ሁሉ ለእኛም የስማችንን ትርጓሜ ከወደፊቱ ስራችን ዕቅድ ጋር እየተነገረን እናድጋለን። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝብን እናዝናናበታለን በሚል ሽፋን የሚወጡ ዘፈኖችም የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው። የአንድን ግለሰብ አስተሳሰብ ለመግለፅ እንዲሁም ለግጥሙ ቤት መድፋት እንጂ ጭብጡ በማኅረሰቡ ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ባለማስተዋል የሚዘፈኑ ዘፈኖች አሉ። “ተበድዬስ ይቅርታ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ” የሚል ዘፈን ሲያዳምጥና አብሮ ሲያንጎራጉር ያደገ ሰው ለይቅርታ ያለው ቦታ ቢያንስ ኸረ እስከ ጭራሹም ባይኖረው ምን ይደንቃል?

ሁላችንም እንደምናስታውሰው በጀግኖች አባቶቻችን ቆራጥ ተጋዳይነት ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሚተርፍ የነፃነት ፋና በዓድዋ ተራሮች ተንቦግቡጎ ባልጠበቀውና ባላሰበው መልኩ ድል የተደረገው የኢጣልያ መንግስት ይህንን በዓለም አቀፍ አደባባይ የውርደት ሸማ ያለበሰውን የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ቂም ለመወጣት በተጠቀመው የመርዝ ጋዝ እጅግ ብዙ ወገኖቻችን በመሪር ስቃይ አልፈዋል። እስቲ እነዚህን የነፃነታችን አምድና ለዛሬው እኛነታችን የሕይወትን መስዋዕትነት ከፍለው ስማቸውን በልባችን ፅላት ላይ በወርቅ ማኅተም ያተሙትን ወገኖቻችንን አንድ ጊዜ ቆም ብለን እናስባቸው። 

በዚያን ጊዜ እነደዚያ ያለውን የጭካኔ ርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘውን አካል ብናገኘውና እጅና እግሩ ታስሮ ፊት ለፊታችን ቢቀርብልን ምን ዓይነት ርምጃ ይሆን የምንወስድበት? እንደው የትኛውን የቅጣት ዓይነት ብንቀጣው ነው አንጀታችን ቅቤ የሚጠጣው? ምን ዓይነት የአገዳደል ስልት ብንጠቀምና ብንገድለው ነው  ያለፈውን የወገኖቻችን ሕይወት፣ የጎደለውን አካላቸውን እና የፈሰሰውን ደማቸውን ዳግም ማግኘት የምንችለው? ቁርጥርጥ አድርገን ብንፈጨውና ወደ አፈር ብንቀይረው ከዚያም ዳግም እንደ ጭቃ አብኩተን ሰውዬውን ሰርተነው እና ሃይሉ ኖሮን እስትንፋስ እንዲኖረው አድርገን እንደገና ብንቆራርጠው ይህንንም ሂደት ሕይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን ቁጥር ብንደጋግመው ስንቶቹን ይሆን ዳግም በሕይወት የምናገኛቸው? ምንም። እርሱ በከፈተው የክፋትና የጭካኔ ጎዳና አብረነው እንድንጓዝ እና እርሱ ለሰራው ጥፋት በሚጠየቅበት ቦታ ብቸኝነት እንዳይሰማው ከማድረግና ከሚከፈለው ክፍያ ተቋዳሽ ከመሆን ያለፈ ጠቀሜታ የለውም።

ታድያ ቂም በቀሉ ፋይዳው ምንድነው? የመንፈስ እርካታ ይገኝበት ይሆን? በቂም በቀል ደስታና እፎይታን ብሎም እርካታን የሚያገኘው መንፈስ እንዴት ያለው መንፈስ ነው? በእውነት ነፍሳችን በእንደዚህ ያለ ድርጊት ደስታን ታገኝ ይሆን? በጭራሽ። ቂም በቀል ጊዜያዊ የሆነ እርካታን ለስጋችን ይሰጠው ይሆናል እርሱም ቢሆን ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ይፀፀታል። ያጣሁትን መልሼ ላላገኝ ይህንን ማድረጌ ምን ጠቀመኝ? ለምንስ የሰነፎችን መንገድ ተከተልኩኝ? እያለ ራሱን መውቀሱ አይቀሬ ነው።  በደልን በበደል፣ ክፋትንም በክፋት፣ ተንኮልንም በተንኮል እንሸፍናለን በሚል የዋህ አስተሳሰብ ታስረን የነገሮችን ውል ከማጥፋት ይልቅ ጥፋትን ተራርሞ ክፍተትን በይቅረታ መሙለቱ የታላቅነትና የአስተዋይነት ብሩሕ ምልክት ነው። ይህ ይቅርታና ይቅር ባይነት መገኛው የት ይሆን?

እንደ እኔ አመለካከት ይቅርታ እና ይቅር ባይነት ምንጩ መንፈሳዊ ሕይወት ነው። ምንም እንኳን ይቅርታ መደራረግ ለስጋዊ ኑሯችንም ታላቅ ጠቀሜታ ቢኖረውም ዋናውና ከዚህ የሚበልጠው ግን መንፈሳዊው ዋጋ ነው። ይህንን መንፈሳዊ ዋጋ ያገኝ ዘንድ ዘወትር የሚተጋ ሰው ልቡናው ለይቅርታ የፈጠነ ነው። በዚህ ምድር በበዳዩ ከተበደለው በደል ይልቅ በሰማይ የሚያገኘው ክብር ሚዛን ይደፋለታል። እዚህ ላይ ግን ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን ነገር አለ። ይቅር ባይነት ቀላል አይደለም እንደማንኛውም ክብርን እንደሚያጎናፅፍ ተጋድሎ ሁሉ እርሱም ከፍተኛ ተጋድሎ ያሻዋል። በአፋችን ለመናገር እንደሚቀለው ያህል ለመተግበሩ ቀላል አይደለም። ይቅር ለማለት ስናስብ ብዙ ፈተናዎች ፊታችን ይጋረጣሉ። ፈተናው ከራስ ይጀምራል የቤተሰብ ፈተናም አለው እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖም አለው። እነዚህን ፈተናዎች በድል አድራጊነት መወጣት የሚችል ሰው ነው ይቅር የሚለው እና ሰማያዊውን ክብር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኘው።

ቁርሾን በሆድ ይዞ ዘወትር መበላላትን፣ መጠፋፋትን እና ልኩን/ለኳን አሳያታለሁ ባይነትን የዘወትር መገለጫው የሆነውን ሰጋችንን ሰማያዊውን ተስፋ አሻግራ ለምትመለከተው ነፍሳችን ስናስገዛ መንፈሳዊነት በሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደተለኮሰ ሻማ ከሩቅ ያበራል። የዚያን ጊዜ የበደሉንን አካላት መጥተው ይቅርታ እስኪሉን ሳንጠብቅ አስቀድመን ይቅርታን እናደርግላቸዋለን። የሰማያዊው ክብር ባለቤቶች መሆናችንን እናውቃለንና ይቅርታውን ባደረግን ወቅት ከመቼውም ይበልጥ ውስጣችን በሐሴት ይሞላል። የሰላም እንቅልፍም እንተኛለን።

ሰሞኑን ሚዲያው ሁሉ ስለ የቀድሞ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከእስር በይቅርታ የመፈታት ሒደት ይዘግባሉ። ስለ እውነት ለመናገር ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩን እንደሰማሁኝ ምንነቱን በውል ባላወኩት ስሜት ውስጥ ገባሁ፤ ቀስ በቀስ ወደ ልቡናዬ ተመልሼ ነገሮችን ከየአቅጣጫው መመልከት ጀመረኩ። በመጀመሪያ ደረጃ በሕይወት እያለሁ ይህንን ዓይነት ከወርቅ የከበረ ታሪክ እጅግ በምወዳት ሀገሬ ለማየት በመታደሌ ሁሉን ቻዩን አምላኬን ቅዱስ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ። ይህንን  ታላቅ ስራ ከመጠንሰስ ጀምረው የተለያዩ ፈተናዎችን አልፈው አሁን ያለበት ደረጃ ያደረሱትን አካላት በሙሉ እስረኞቹን፣ በደል የደረሰባቸው እና በአንድም በሌላ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና መንግስትን በእውነት ምስጋና ይገባቸዋልና አመሰገንኳቸው።

በተለይ በተለያየ መንገድ ለተለያየ ስቃይና መከራ ለተዳረጉት ወገኖቻችን ይህንን ይቅርታ ማድረግ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን መቼም አያጠያይቅም። ይቅርታውን ማድረጉ ሳይሆን ገና ሲታሰብ እንኳን የቱን ያክል ስሜትን እንደሚረብሽና በስርዓቱ ወቅት ያጣነው ነገር ሁሉ በዓይነ ሕሊናችን እየመጣ እንደሚያስቸግረን እሙን ነው። እዚህ ላይ ልታስተውሉት የሚገባው ነገር በወቅቱ በደረሰው ጥቃት በደል የደረሰበት ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን እንዲሁም ይህ ጉዳይ በእናንተ ይቅር ባይነት መጠናቀቁ በምድርም በሰማይም አሸናፊዎቹ እናንተ እንደሆናችሁ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚፈፀምና በተለይ ለእናነተ በታሪክ የክብር ባለቤት  ያደርጋችኋልና ልትኮሩ ይገባችኋል። ለትውልድ መተላለፍ ያለበት ምን መሆኑን ለሁላችንም አስተምራችሁናልና በድጋሜ ላመሰግናችሁ አወዳለሁ።

የሃይማኖት አባቶች እየሰራችሁት ያለው ነገር በእጅጉ የሚያስመሰግናችሁና ከዚህ በፊት ከእናንተ አጥተነው የነበረ በመሆኑ ጅምራችሁን ከፍፃሜ እንድታደረሱና በቀጣይም እንዲህ ዓይነቱን ስራ አበርትታችሁ እንድትቀጥሉበት  አደራዬ የጠበቀ ነው። መንግስትም እንዲሁ እንዲህ ያለ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፈት በመፍቀዱና ለተግባራዊነቱም ያሳየው ተነሳሽነት በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው። ውጤት ተኮር ስራ ማለት እንደዚህ ነው።

በጅምር ላይ ያሉ ስራዎች ከፍፃሜ ደርሰው እንድናያቸው እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን።
ቸር ያሰማን፤ አሜን።


 
በገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ

ያዘቀጠው አሰር እየደፈረሰ
የተቀጣጠለው. . . እንጨቱ እየጨሰ
መሬት ቁና ሁና የሰው ልጅ ሲጨንቀው
እሳት ተያይዞ አገሩን ሲያለብሰው
ባለቤት ተሰዶ አዱኛ ፈራርሳ
አሞራ ሲያንዣብብ ተከምሮ ሬሳ
ስጋ ሲርበደበድ. . . ነፍስ ይሽቆጠቆጣል
ያኔ እያቀዘፈው ደም ይገነፍላል፡፡
ኮሽ ባለ ቁጥር ዞሮ ሲገላመጥ
እየተንሻተተ ገደሉን ሲባጥጥ
ሲቃትት ሲደክም ሲርበው ሲጠማው
ስጋውን በመካድ ሞትን ይመኛል ሰው፡፡
የፍቅር ጥላ ነው  ጭጋግ የደስ. . .ታ
ሀዘን መንገላታት፤ መታሰር መቸገር
    መቁሰል መሰቃየት የሌለው
ፀጥታ

ያንድነት እከክ ነው ልብሱ የነተበ
በላብ በጭቅቅት ገላው የረጠበ
ተለዋዋጭ መልኩ ያልታወቀ ግቡ
አልቋል ሞቷል ሲሉት ያው ይነትራል ልቡ፡፡
ስጋ ተለያይቶ ሲቀር አጥንታቸው
ማንንም በስሙ መጥራት የማንችለው
መልካቸው ሲጠፋ ሁነው እንዳልነበር
እነሆ ርስታቸው የእኩል ቤት መቃብር፡፡
መድፍ የተከላቸው መትረየስ ዘርዝሮ
ቦምብ የመገባቸው አውሮፕላን በሮ፤
ታንክ በደነጎረው ጠመንጃ ዘርቷቸው
ጢስ ወሀ እየሆነ ሲጠጡ ባፋቸው
የታል የበቀሉት ወዴት ነው ቦታቸው?
ሐውልቱ ድንጋዩ ምን አጎነቆለ
     ባንድ በኩል ደግሞ
     የሰላም ሚዛን ነው
     የበዛን አረም
     የሚያስተካክለው፡፡
ሰላም ብዙ ሲቆይ ስሩ ያሻግታል
መሰረቱ ዝጎ ቀስ ብሎ ይወድቃል፤
አንስቶ በመካብ የፈራረሰውን
ቀብሮ በመለሰን. .  .ሲያድስ መሰረቱን፤
ኃይለኛ ሲገባ ሲከተል ዓላማ
ባለህ እርጋ ብሎ አዋጁን ሲያሰማ፤
ይኸው ተጀመረ አዲስ ዓይነት ሰላም
ዳግመኛ እስቲወድቅ ፈርሶ እስቲደመደም፤
ሰላም ያቻት ብሎ ሁሉም የሚጮኸው
ክፉ ቀን አታምጣ ብለን የምንተቸው
በፀሎታችን ውስጥ መሪ እንዳያሳጣን
ወድቀን እንዳንቀር ተገዥ በመሆን፤
ያችት ዓላማችን ነፋስ ተቀበላት
ብለን የምንቆመው ሰላም የምንላት
ፀጥታ ሲኖር ነው አልፈን በጦርነት፤
አንደኛው ሲተኛ ያኛው ሲጠበቀው
ሰላም ወይ ጦርነት ድርና ማግ ናቸው፡፡

ያዘቀጠው አሰር እየደፈረሰ
የተቀጣጠለው. . . እንጨቱ እየጨሰ
መሬት ቁና ሁና የሰው ልጅ ሲጨንቀው
እሳት ተያይዞ አገሩን ሲያለብሰው
ባለቤት ተሰዶ አዱኛ ፈራርሳ
አሞራ ሲያንዣብብ ተከምሮ ሬሳ
ስጋ ሲርበደበድ. . . ነፍስ ይሽቆጠቆጣል
ያኔ እያቀዘፈው ደም ይገነፍላል፡፡
ኮሽ ባለ ቁጥር ዞሮ ሲገላመጥ
እየተንሻተተ ገደሉን ሲባጥጥ
ሲቃትት ሲደክም ሲርበው ሲጠማው
ስጋውን በመካድ ሞትን ይመኛል ሰው፡፡
የፍቅር ጥላ ነው  ጭጋግ የደስ. . .ታ
ሀዘን መንገላታት፤ መታሰር መቸገር
    መቁሰል መሰቃየት የሌለው
ፀጥታ
ያንድነት እከክ ነው ልብሱ የነተበ
በላብ በጭቅቅት ገላው የረጠበ
ተለዋዋጭ መልኩ ያልታወቀ ግቡ
አልቋል ሞቷል ሲሉት ያው ይነትራል ልቡ፡፡
ስጋ ተለያይቶ ሲቀር አጥንታቸው
ማንንም በስሙ መጥራት የማንችለው
መልካቸው ሲጠፋ ሁነው እንዳልነበር
እነሆ ርስታቸው የእኩል ቤት መቃብር፡፡
መድፍ የተከላቸው መትረየስ ዘርዝሮ
ቦምብ የመገባቸው አውሮፕላን በሮ፤
ታንክ በደነጎረው ጠመንጃ ዘርቷቸው
ጢስ ወሀ እየሆነ ሲጠጡ ባፋቸው
የታል የበቀሉት ወዴት ነው ቦታቸው?
ሐውልቱ ድንጋዩ ምን አጎነቆለ
     ባንድ በኩል ደግሞ
     የሰላም ሚዛን ነው
     የበዛን አረም
     የሚያስተካክለው፡፡
ሰላም ብዙ ሲቆይ ስሩ ያሻግታል
መሰረቱ ዝጎ ቀስ ብሎ ይወድቃል፤
አንስቶ በመካብ የፈራረሰውን
ቀብሮ በመለሰን. .  .ሲያድስ መሰረቱን፤
ኃይለኛ ሲገባ ሲከተል ዓላማ
ባለህ እርጋ ብሎ አዋጁን ሲያሰማ፤
ይኸው ተጀመረ አዲስ ዓይነት ሰላም
ዳግመኛ እስቲወድቅ ፈርሶ እስቲደመደም፤
ሰላም ያቻት ብሎ ሁሉም የሚጮኸው
ክፉ ቀን አታምጣ ብለን የምንተቸው
በፀሎታችን ውስጥ መሪ እንዳያሳጣን
ወድቀን እንዳንቀር ተገዥ በመሆን፤
ያችት ዓላማችን ነፋስ ተቀበላት
ብለን የምንቆመው ሰላም የምንላት
ፀጥታ ሲኖር ነው አልፈን በጦርነት፤
አንደኛው ሲተኛ ያኛው ሲጠበቀው
ሰላም ወይ ጦርነት ድርና ማግ ናቸው፡፡