Friday, April 12, 2013

 አንድ ምሁር በገበሬው ፊት





አንድ በእርሻ ላይ የሚሠራ ዪኒቨርሲቲ መምህር በገበሬው ዙርያ ጥናት ለመሥራት ወደ ገጠር ወጡ፡፡ የአካባቢው የገበሬዎች ማኅበርም በአካባቢው የሚኖሩትን ገበሬዎች ለጥናቱ እንዲተባበሩ ለማድረግ ስብሰባ ጠራ፡፡ ምሁሩም ከገበሬዎቹ ፊት ለፊት ተቀመጡና ስለመጡበት ሥራና ከገበሬዎቹ ስለሚጠበቁ ነገሮችም ማብራራት ጀመሩ፡፡
‹‹ጉድ አፍተርኑን፤ እዚህ የመጣነው ፍሮም ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከእናንተ ጋር ሚት ማድረጋችን ጉድ ኦፖርቹኒቲ ነው፡፡ ኦፍ ኮርስ እዚህ ለመምጣት ያሰብነው ቢፎር ኤ ይር ነበር፡፡ በት አንዳንድ ፕሮሲጀሮችን ለማሟላት ሃርድ ስለሆነብን ትንሽ ሌት ሆነናል፡፡ ሶሪ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሜይን ኢንካሟ አግሪካልቸር መሆኑን አንደርስታንድ ታደርጋላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አግሪካልቸር ዋን ኦፍ ዘ ሜይን የሰው ልጆች አንሸንት አክቲቪቲዎች ነው፡፡ ኢን ኢትዮጵያ ደግሞ ሎንግ ሂስትሪ አለው፡፡ በት አግሪካልቸራችን አንደር ደቨሎፕ ሆኗል፡፡ ፋርሚንጋችን ፑር ነው፡፡ አክቲቪቴያችን ሌበረስ ነው፡፡ ገበሬው ሳይንቲፊክ ዌይ አይጠቀምም፡፡ ፋርሚንጋችን ሜካናይዝድ አይደለም፡፡ ገበሬው ኢንፎርሜሽን እንደልቡ አያገኝም፡፡ 
ናው እኛ ሪሰርች የምንሠራበት ኤርያ ገበሬው ሃው ካን አቺቭ ዘኒው ቴክኖሎጂ በሚለው ዙርያ ነው፡፡ ከእናንተ ፉል ፓርቲሲፔሽን እንፈልጋለን፡፡ አይ ሆፕ ኮኦፐሬቲቭ ትሆናላችሁ፡፡ ያዘጋጀናቸው ኩዌሽነሮች አሉ፡፡ ለእነዚህ ኩዌሽነሮች ኢንፎርሜሽን ትሰጡናላችሁ፡፡ ከእናንተ መካከል ራንደምሊ ኢንፎርማንቶችን እንወስዳለን፡፡ ሳም ኦፍ ዩ ሳትመረጡ ብትቀሩ ደስፐሬት እንዳትሆኑ፡፡ ኢን አዘር ዌይ እናገኛችኋለን፡፡
እነዚህን ኢንፎርሜሽኖች ወሰደን ዳታዎቹን የእናንተን ላይፍ ለማስተካከል እንጠቀምበታለን፡፡ ኢሪጌሽን ላይና አኒማል ሀዝባንደሪ ላይ ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው፡፡ አፍተር ዛት ደግሞ ሌሎች ላይ እንሄድባቸዋለን፡፡
ታንክ ዩ ለትብብራችሁ፡፡
ገበሬዎቹ አላጨበጨቡም፤ ራሳቸውንም አልነቀነቁም፡፡
የገበሬ ማኅበሩ ሊቀ መንበር ‹‹እስኪ ጥያቄ ያላችሁ?›› አሉ፡፡ ገበሬዎቹ ዝም አሉ፡፡ ሊቀመንበሩ ደጋግመው ቢጎተጉቱም ገበሬዎቹ ጸጥ አሉ፡፡ በመካከል አንዲት እናት ተነሡና፡፡
‹‹እስኪ የመጡት ሰውዬ ይናገሩና እንጠይቃለን›› አሉ፡፡
ሊቀ መንበሩ ግራ ገባቸውና ‹‹እርሳቸውማኮ ተናገሩ›› አሉ፡፡
‹‹እኛ ግን አልሰማናቸውም›› አሉ እኒያ እናት፡፡
‹‹ታድያ እስካሁን ምን ያደረጉ ነው የመሰላችሁ›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡
‹‹እኛማ በማናውቀው ቋንቋ የመክፈቻ ጸሎት እያደረሱ ነው የመሰለን›› አሉ፡፡
from dagi views

No comments:

Post a Comment